ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት( ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም): የዩኔስኮ የቅርስ ጥበቃ ኮንቬንሽን አባል አገራት ጠቅላላ ጉባኤ ሕዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ አባል አገር አድርጎ መርጧል፡፡

ኢትዮጵያ ተወዳድራ የተመረጠችው ለማንኛውም አህጉራዊ ክልል ላልተሰየመ ክፍት ቦታ ሶሆን ፣ ከ168 መራጭ አባል አገራት የ125ቱን ድምፅ ለማግኘት ችላለች፡፡

የዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ 21 አባላት ያሉት ሲሆን የቅርስ ጥበቃ ኮንቬንሽንን የመተግበር፣ የዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃ ፈንድ አጠቃቀምን የመወሰን፣ ለአገራት የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመዘገቡ ቅርሶችን የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡

በኮሚቴው ውስጥ ኢትዮጵያ ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ለቅርስ ምዝገባና ጥበቃ በተለይም በአህጉራችን የሚገኙት ቅርሶች ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙ ትንቀሳቀሳለች፡፡

ኢትዮጵያ ስምንት የባህል እና አንድ የተፈጥሮ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አስመዝግባለች፡፡ይህንን ምርጫ ተከትሎ አገራችን በተመሳሳይ ወቅት የሁለቱ ዋና የዩኔስኮ አካላት ማለትም የአስፈጻሚ ቦርድና የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ አባል ሆና ታገለግላለች፡፡