የአቡነ ገሪማ ገዳም

የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የገባው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ይሁን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋው ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ በተስኣቱ ቅዱሳን እንደሆነ እምነቱን ለማስረፅ በሸለቆዎች፣ በሰዋራና ጭር ባሉ አካባቢዎች ጭምር አብያተክርስቲያን በመስራት ወንጌልን ሰብከዋል፡፡ ከእነዚህ ተስኣቱ ቅዱሳን አቡነ ገሪማ አንዱ ናቸው፡፡ በእኝሁ ፃድቅ ስም የሚጠራው ገዳም በአፄ ገ/መስቀል በ520 አካባቢ ተመስርቶ እስካሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ገዳም በተለይ የሚታወቀው አቡነ ገሪማ እንደፃፉት የሚታመንበት እና በግእዝ ቋንቋ በተፃፈው አርባእቱ ወንጌል ነው፡፡

የአባ ገሪማ ወንጌል የ1483 ዓመት ዕድሜ እንዳለው በሳንሳዊ መንገድ ተረጋግጧል፡፡ እስካሁን በዓለም ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ጥንታዊ የሆነ መንፈሳዊ መፅሃፍ እንዳልተገኘ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ወንጌሉ በግዕዝ ቋንቋ በፍየል ቆዳ ላ እነደተፃፈና ራሳቸው አባ ገሪማ ሊፅፉት እንደቻሉ ማስረጃዎች አሉ ይላል የጥናቱ ቡድን፡፡ “የአባ ገሪማ ወንጌል” እየተባለ በገዳሙ የሚጠራው ይኸው ጥንታዊ መፅሃፍ የወንጌላውያኑን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሃንስ ክፍሎች አንድ ላይ አጣምሮ ይዟል፡፡ አፃፃፉ፣ ቀለሙና የስዕሉ አወዳደቅ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ አስችሎታል፡፡ ይህ መፅሃፍ ወርቅ በተቀባ ሽፋን የተሰራ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡        

በአራት ረዣዥም ተራሮች የተከበበው የአቡነ ገሪማ ገዳም የታላቁ አፍሪካዊ ጀነራል የራስ አሉላ አባነጋ  አስከሬን ያረፈበት ከመሆኑ ሌላ በአድዋ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ጦር መሽጎበት የነበረ ቦታም በመሆኑ ልዩ ክብር አለው፡፡ ከዚህ ሌላ ዙሪ ገባውን በደን የጠሸፈነና በተለያዩ ህብረ ቀለም ያሸበረቁ ወፎች መጠለያ በመሆኑ ይበልጥ ማራኪ ያደርገዋል፡፡

ምንጭ፡ የትግራይ ቱሪዝም መፅሔት