የአዲ አካውሕ አርኪዮሎጂ ስፍራ ከውቕሮ ከተማ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 8 ኪ.ሜ ያህል ርቆ ይገኛል፡፡ ይህ ስፍራ በአካባቢው አፈ-ታሪክ “መቃብር ጋዕዋ” ተብሎ ሲጠራ የዮዲት ጉዲት ወይም በአካባቢው መጠሪያ ስሟ “ጋዕዋ” መቃብር እንደሆነና መርዛማ መዥገሮች እንዳሉበት የሚነገርለት አስፈሪ ስፍራ ነበር፡፡ ሆኖም በባለሙያሙያዎች በተደረገ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ዓዲ አካውሕ የሴት ምስል የያዘ ሃውልት፣ በጥንታዊው የሳባውያን ፅሁፍ የተዋበ የመስዋዕት ድንጋይ እና ለመስዋዕት አገልግሎት አገልግሎት እንደዋሉ የታመነባቸው የአጥንትና ከሰል ስብርባሪ እንዲሁም የህንፃ መሠረት የተገኘ ሲሆን በስፍራው ቀጣይ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡

እስካሁን ባለው የጥናት ውጤት በተለይ ፕሮፌሰር ኖበርት ነቢስ የተባሉ ተመራማሪ በተገኘው የሳባዊያን ፅሁፍ ላይ ባካሔዱት የትርጉም ሥራ አካውሕ የ”አልሙቃህ” ቤተ አምልኮ የነበረ ሲሆን “ዋዕራን ኢብን ራድእ” የተባለ ንጉስ እንዳሰራው ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ስፍራ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ “የሓ” የሚል ቃል በሳብያን ቋንቋ ተፅፎ እንደተገኘ ፕሮፌሰሩ ይገልፃሉ፡፡ በዚህ ግኝት መሠረት ይህ ስፈራ የሓና ሐውልት መላዞ ከመሳሰሉት የቅድመ አክሱም ስልጣኔ አሻራዎች ጋር የሚመደብና ከ8ኛው እስከ 7ኛው ዓ.ዓ የነበረው የዳአማት ስርወ መንግስት ቤተ አምልኮ መሆኑ ይታመናል፡፡

ምንጭ፡- የት/ብ/ክ/መ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ