የአሕመዲን ነጃሽ መካነ መቃብር ከመቀለ ወደ ዓዲግራት በሚወስደው አውራ መንገድ ከውቅሮ ከተማ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በተራራ አናት በተቆረቆረ ትንሽ ከተማ ላይ ይገኛል፡፡ የአህመዲን ነጃሽ መካነ መቃብር ታሪክ ነብዩ መሐመድ ተከታዮቻቸው ወደ ሐበሻ ምድር እንዲሰደዱ ከላክዋቸው ጊዜ ጀምሮ አንድ ተብሎ የቆጠራል፡፡ ስደተኞቹ በሁለት ሂጅራ (ጉዞ) ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን ጊዜውም እ.ኤ.አ በ615 ነበር፡፡ ነብዩ መሐመድ በሃገራቸው እስልምና በሚያስተምሩበት ወቅት ተከታዮቻቸው ቁረይሽ በተባለ የዚያው አገር ጎሳ አባላት እየታደኑ ይገረፉና ይገደሉ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ በነጃሽ ከተማ አንድ ትልቅ መስጊድ፣ ሁለት ደሪሖች /አስከሬን ያረፈባቸው ህንፃዎች/ እንዲሁም በርካታ  መቃብሮች ይገኛሉ፡፡ ይህ በሃገራችን በቅድስነቱና በቀደምትነቱ የሚታወቀው ስፍራ በዓለም ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ዕውቅናና ክብር የተጎናፀፈና ሁለተኛ መካ በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ የመስጊዱና የመቃብሩ ዓመታዊ በዓል ቀን በዓረቦች አቆጣጠር መሃረም 10 ቀን ወይም በዓሹራ በትልቅ ድምቀት ይከበራል፡፡

 

ምንጭ፡- ትግራይ ቱሪዝም መፅሔት