ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት (ሐምሌ 2011 ዓ.ም)፡ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኢጋድ ልኡካን ቡድንን ዛሬ ሀምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ በኢጋድ-የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዶ/ር ኢስማዒል ዋዓይስ፣ የአርጄሜክ (Reconstituted Joint Monitoring and Evaluation Commission) ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሌ/ጄነራል ኦጎስቲኖ እንዲሁም የሲቲሳም (Ceasefire and Transitional Security Arrangements Monitoring Mechanism in South Sudan (CTSAMM) ተ/ሊቀመንበር ሜ/ጄነራል ደስታ አቢቸ ተገኝተዋል። 

ውይይቱ በጁባ 67ኛው የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች እና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ እና የሰላም ሂደቱ አፈፃፀም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የልኡካን ቡድኑ ለክቡር ሚኒስትሩ አስረድተዋል። በቀጣይም የኢጋድ አባል ሀገራት በስምምነቱ መሰረት ለትግበራው አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ የቡድኑ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢጋድ ሊቀመንበርነት ባላት ሚናና እንደጎረቤት ሀገርም ደቡብ ሱዳን ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ  ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢጋድ ለስምነቱ ተግባራዊነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።