ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት (ነሐሴ 2011 ዓ.ም)፡ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት እና በነጻነት እና ለውጥ ኃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር የሽግግር ሕገ መንግስት እና የፓለቲካ ስምምነት በመፈራረም መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ሕብረት ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ላበረከቱት አስተዋጽኦና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም የምስጋና ፕሮግራም በማዘጋጀት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ዳይሬክተር ጄኔራሎች በተገኙበት ሽልማት አበርክቷል።

ሽልማቱ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሱዳን ልዩ ልዑክ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር ፣ለክቡር በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ እና የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ መሃመድ ሃሳን ላባት የተበረከተ ሲሆን፣ የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት የፓለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ ጄኔራል ሸምሰዲን አል ካባሺ በተገኙበት የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦስማን ዳሃብ ሽልማቱን አበርክተውላቸዋል።

የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦስማን ዳሃብ በሽልማት ስነ ስርአቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን እና የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሲካሄድ በቆየው የድርድር ሂደት በአደራዳሪነት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የምስጋና ሽልማቱ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና በቀጣይ በሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በተለያዩ የትብብር መስኮች ለሚከናውኑ ተግባራት ጥረት መልካም መደላድል እንደሚፈጥር ይታመናል።