የመጀመርያው በውጭ ባለሃብቶች የተቋቋመ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 2፣ 2011 – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮ ሊዝ የስራ ፈቃድ ሰጠ፡፡ ይህ ፈቃድ
ኢትዮ ሊዝን የመጀመሪያው በውጭ ሃገር ባለሀብቶች የተቋቋመ የፋይናንስ ተቋም ያደርገዋል፡፡ ኢትዮ ሊዝ
በዋናነት በአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (ኤ. ኤ. ኤፍ. ሲ) የተቋቋመ ነዉ፡፡ ኤ. ኤ. ኤፍ. ሲ ዋና መስሪያ
ቤቱ በአሜሪካ የሚገኝ የግል ኢንቨስትመንት ኩባንያ ሲሆን በመላው አፍሪካ የተለያዩ የብድር እና የካፒታል
ዕቃዎች ኪራይ (ሊዝ) አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ድርጅት ነዉ፡፡

ኢትዮ ሊዝ በይፋ ነሀሴ 2፡ 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የገንዘብ ሚኒስቴሩ
የተከበሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የኢትዮ ሊዝ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ግርማ ዋቄ፣ የኢትዮ ሊዝ አመራሮችና
የስራ ኃላፊዎች፤ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሸራተን አዲስ ሆቴል በይፋ
ተከፍቷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን “ኢትዮ ሊዝ የመጀመርያው በውጭ ሃገር
ባለሀብቶች የተመሰረተ የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ንግድ ተቋም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ትልቅ
ተሳትፎ እንደሚኖረውና ለኢኮኖሚዉ ዕድገትም ሚና እንደሚኖረዉ፤ እንዲሁም ለአገሪቱ የዉጭ ምንዛሪ
የገቢ ምንጭ አስተዎፅኦ እንደሚያደርግ እናምናለን” ብለዋል፡፡

የፋይናስ ሚኒስተሩ የተከበሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሲናገሩ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አሕመድ
በዳቮስ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ የፋይናስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት እንደምትከፍት ቃል
በገቡት መሰረት ይህን የመጀመርያውን በውጭ ሃገር ባለሀብቶች ባለቤትነት የተቋቋመዉን የፋይናስ ተቋም
በኢትዮጵያ ስራ መጀመር አስመልክቶ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫዉ ላይ የተገኙት የአሜሪካን አምባሳደር ማይክል ሬይነር በበኩላቸዉ ሲናገሩ “ኢትዮ
ሊዝ ለኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ከፍተኛ እድል ይዞ የመጣ ነዉ፡፡ ይህም በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር፣
በዘመናዊ ቴክቶሎጂ የተደገፉ የእርሻ፣ የማምረቻ፣ የኮንስትራክሽን እቃዎች እንዲሁም አስተማማኝ የፋይናስ
ሞዴል የሚጠቀም እና በኢትዮጵያ የእዳ ጫና ላይም ጉልህ ጭማሪ ሣያመጣ የሚሰራ መሆኑ ነዉ፡፡ ይህም
አሜሪካ በኢትዮጵያ የምታደርጋቸዉ ኢንቬስትመንቶች ሁነኛ ምሳሌ ነዉ” ብለዋል፡፡

ይህ የካፒታል ዕቃዎች አከራይ ድርጅት (ኢትዮ ሊዝ) ስራ የጀመረበት ጊዜ ደግሞ በኢትዮጲያ የካፒታል
ዕቃዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉበትና የዉጭ ምንዛሪ እጥረት ያለበት ጊዜ በመሆኑ፣ ኢትዮ ሊዝ እነዚህን
ለማቃለል የሚረዳ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ኢትዮ ሊዝ ለበርካታ ሴክተሮች ማለትም ለግብርና፣ ለጤና፣
ለምግብ ማቀነባበሪያ (ቡናን ጨምሮ)፣ ለኃይል አቅርቦት፣ ለማምረቻና ለመሳሰሉት የተለያዩ የካፒታል
ዕቃዎችን በኪራይ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

የኢትዮ ሊዝ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ግርማ ዋቄ ስለ ኢትዮ ሊዝ መከፈት አስመልክቶ ሲናገሩ “ጥራት
ያላቸውን የካፒታል ዕቃዎች በኪራይ በማቅረብ ኢትዮጲያ ውስጥ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
ድርጅቶች ለካፒታል ዕቃዎች ግዢ የሚያወጡትን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ለሌሎች ስራዎቻቸዉ ማለትም
ለጥሬ ዕቃ መግዣና ለስራ ማስኬጃ በማዋል የተከራዩት የካፒታል ዕቃ ከሚያስገኘዉ ገቢ ኪራዩን እየከፈሉ
እንዲገለገሉበት ያስችላቸዋል፡፡ ይህም ገንዘባቸዉ በካፒታል ዕቃዎች ላይ እንዳይታሰር ያደርጋል” ብለዋል፡፡

ኢትዮ ሊዝ የካፒታል ዕቃዎችን በራሱ ካፒታል ገዝቶ በረዥም ጊዜ ማለትም በካፒታል ዕቃዎቹ የኢኮኖሚ
ዕድሜ (economic life) ኪራይ በማስከፈል ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲገለገሉባቸዉ የሚያደርግ ሲሆን፣
ተከራዮቹ ዕቃዎቹን በአግባቡ መጠቀማቸዉን፣ የዕቃዉን ጥገና፣ ጤንነት እና ደህንነት ይከታተላል፡፡

የኢትዮ ሊዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ግሩም ፀጋዬ በበኩላቸዉ የካፒታል ዕቃዎች ኪራይን ጠቀሜታ
በተመለከተ ሲያብራሩ “የካፒታል ዕቃዎቹን በዉጭ ምንዛሪ ገዝተን በማቅረብና ከተከራዮቹ በኢትዮጵያ
ብር ኪራዩን የምንቀበል ይሆናል” ብለዉ ኢትዮ ሊዝ በውጭ ባለሃብቶች ኢንቬስትመንት የተቋቋመ በመሆኑ
የዉጭ ምንዛሪ ዕጥረት የሌለበት እና የራሱን የዉጭ ምንዛሪ የሚጠቀም መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም
“የኪራይ ዉሉ ሲያበቃ ተከራዩ አስቀድሞ በኪራይ ዉሉ ዉስጥ በተጠቀሰ የሽያጭ ዋጋ ዕቃዎን መግዛት
የሚችልበትን አማራጭ ዕድል ይሰጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እትዮ ሊዝን በማቋቋሙ ሂደት በ.እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ የካፒታል ዕቃዎችን ፍላጎት፣ የአቅርቦት ሰንሰለት
እና እጅግ ዉስብስብ የሆኑትን የዘርፍን ህጎችና የቁጥጥር መመሪያዎች ለመረዳት ሰፊና ረዥም ጊዜ የፈጀ
ጥናት አካሂዷል፡፡ አሁን አስፈላጊዉን የስልትና ዕቅድ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

የኢትዮ ሊዝ ምክትል ሊቀመንበር ሚ/ር ፍራንስ ቫንሽአይክ ስለ ኢትዮ ሊዝ ሲናገሩ “የካፒታል ዕቃዎች
ሊዝ በሰለጠነዉ አለም ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት የሚታይበት ሲሆን፣ በአሜሪካ ብቻ እንኳ የትሪሊዮን ዶላር
ንግድ ከመሆኑም ባሻገር ከ75% በላይ የሚሆኑ ዕቃዎች በኪራይ አሰራር ስራ ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ በተቃራኒዉ
በአፍሪካ 5% የሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ብቻ ናቸዉ በዚህ አሰራር የሚጠቀሙት፣ ከነዚህም ከሚጠቀሱት
ደቡብ አፍሪካ ፣ ናይጄሪያ እና ሞሪሸስ ናቸው” ብለዋል፡፡