ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት (ነሐሴ 2011 ዓ.ም)፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ የጃፓን መንግስት የዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ተጠሪና የቶክዮ ኮንፈረንስ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ) አምባሳደር ኦካሙራ ዮሺፉሚን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያና ጃፓን ረጅም የወዳጅነት ታሪክ የሚጋሩ ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በኋላ በጃፓን በሚካሄደው የቲካድ ሰባተኛ ጉባኤ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ እንደምትገኝ አሳውቀዋል፡፡ ጉባኤው ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የቀረበ ግንኙነት የሚመጥን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማድረግ አይነተኛ መድረክ እንደሚሆን ያላቸውንም ተስፋ ገልጸዋል፡፡ 

ክቡር ኦካሙራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ድምጽ አድርገው እንደሚቆጥሯትና ሰባተኛው የቲካድ ጉባኤ ከሚያቀርባቸው ዘርፈ ብዙ የቢዝነስ እድሎች ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በዋናነት በርካታ የግዙፍ ኩባንያ መሪዎች በጉባኤው እንደሚሳተፉ የገለጹት ተጠሪው ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለማበረታት የወሰደቻቸውን የኢኪኖሚ ሪፎርሞች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡

የቶክዮ ኮንፍረንስ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ) እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም በጃፓን መንግስት አዘጋጅነት የተጀመረ ጉባኤ ሲሆን የአፍሪካን ልማት እንዲሁም ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የባለብዙ ወገን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር ያለመ መድረክ ነው፡፡