ሀገራችን ባላት ድንቅ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እና የተለያየ የአየር ንብረት የተነሳ የልዩ ልዩ የዱር እንስሳትና እፅዋት ዝርያዎች መኖሪያ ልትሆን ችላለች፡፡ ይህም በ1956 ዓ.ም በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መሠረት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) በመጡ ባለሙያዎች የተደረገውን አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ተከትለው በተከናወኑ የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮች ተረጋግጧል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች በአገራችን በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የዱር እንስሳት ዝርያዎች እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን ከእነርሱም መካከል ከ200 በላይ የሚሆኑት በአገራችን ብቻ የሚገኙ (Endemic Species) ናቸው፡፡ ይህን እውነታ በተሻለ ለመረዳት ይቻል ዘንድ ከዚህ በታች ባለው ሠንጠረዥ ላይ ዘርዘር ብሎ ቀርቧል፡፡

የምድብ ስም የዝርያዎች ብዛት የብርቅዬ ዝርያዎች ብዛት
ጡት አጥቢ 284 31
አእዋፍ 862 17
ተሳቢና ተራማጅ (ሬፒታይልስ) 201 14
በውሃና በመሬት ላይ የሚኖሩ (አምፊቢያንስ) 64 30
ዓሳ 150 4
ነፍሳት (አርትሮፖድስ) 1225 7 (ቢራቢሮ)
ድምር 2786 203

እንዲሁም ከ7000 በላይ የተለያዩ “ከፍተኛ” የእፅዋት ዝርያዎች (Higher Plant Species) በአገራችን እንደሚገኙ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን ከእፅዋቱም መካከል ከ10 እስከ 12 ፐርሰንት የሚሆኑት በአገራችን ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን